Home
Welcome to the Frontpage
“ተንሥአ በከመ ይቤ -- እንደተናገረው ተነሥቷል” PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Saturday, 18 April 2020 12:44

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

“ተንሥአ በከመ ይቤ -- እንደተናገረው ተነሥቷል”

ማቴ ፳፰፥፮

መጋቤ ምሥጢር ዶ/ር ኅሩይ ኤርምያስ


ክርስቶስ በደሙ የዋጃችሁ ለሰማያዊት መግሥቱም

ወራሽነት የጠራችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር የዓለማት

ፈጣሪና ገዥ የሆነው አምላካችን እንኳን በሰላምና በጤና

ጠብቆ ለመድኅነ ዓለም ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፤

በዓሉ የሰላም፣የደስታና የበረከት በዓል ይሁንላችሁ።


የክርስቶስ ትንሣኤ ጠላት ዲያብሎስ ያፈረበት የሰው

ልጅ የከበረበት፤ ሐሰትና ዐመጽ የተንኮታኮተበት እውነት

የነገሠበት፤ አዳኙ ሰይጣን የታሰረበት እስረኛው አዳም

ከነልጅ ልጆቹ ነፃ የወጣበት፤ ሞት ተዋርዶ ሕይወት

የሠለጠነበት በመሆኑ በክርስትና ሃይማኖት

መሠረትነት ከሚከበሩ በዓላት ሁሉ በክብርም

በኅብርም እጅግ ከፍ ያለና የከበረ በዓል ነው።


ከአምስት ሺህ ዘመን በላይ የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ ሆኖ

የኖረውና በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው የመንፈስ ምኞት

ወድቆ የነበረው የሰው ልጅ መነሣት” እውን የሆነው

ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ዓመት በፊት

በኢየሩሳሌም ከተማ በዕለተ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት

በተፈጸመው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው።


ከሰማየ ሰማያት የወረደበትን ሥጋና ነፍስን ከቅድስት

እናቱ ተዋሕዶ ሰው የሆነበትን በጎ አሳብና አምላካዊ

ቸርነት ለመፈጸም በዕለተ ዓርብ በመስቀል ተሰቅሎ

ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው የለየው የዓለሙ ተስፋ

ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ ለደቀመዛሙርቱ በጸሐፍትና

በሊቃነ ካህናት ዘንድ የሚቀበለውን መከራ ሲነግራቸው

ከሞት በኋላ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ

እንደሚነሣም ነግሯቸው ነበረ። ማቴ ፲፮፥፳፩ ዮሐ ፪፥፲፱-፳፩


ሁሉን ትተው ለተከተሉትና የዓለም ባይተዋሮች ለሆኑ

ደቀመዛሙርት እንዲህ ያለውን የሞት ዜና መስማት

ለዚያውም ከራሱ ከሚሞተው ጌታ አንደበት - ምንኛ

አስጨናቂ ነው! ዳሩ ግን ጌታ ሰው የሆነበት ዓላማው

ጌዚያዊና ምድራዊ ደስታን ለጥቂት ሰዎች ማስገኘት

ሳይሆን የማያልቅ የማይጠፋ መንፈሳዊና ነፍሳዊ

ሐሤትን ለዓለሙ ሁሉ መስጠት ስለሆነ እንደ ወንጀለኛ

በወታደሮች ታሥሮ በሸንጎ ቆመ፤ ምራቅ ተተፋበት፣

ተዘበተበት፣ ፊቱን በጥፊ ራሱን በመቃ ተመታ፣ ሥጋው

አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር በጅራፍ ተገረፈ በመጨረሻም

ከልብስ ተራቁቶ በመስቀል ላይ ተሰቀለ።

ማቴ ፳፯፥፴፭ ሉቃ ፳፫፥፴፫


በኀጢአት ምክንያት ለሞት የተገዛ የሰውን ባሕርይ ከሞት

አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ራስን ለሞት አሳልፎ መስጠት

ምንኛ ድንቅ ነው? በበደል ምክንያት ጣዕመ ጸጋ ያጣ የሰውን

ልጅ ሕይወት በመንፈስቅዱስ ጸጋ ለማጣፋጥ አንጀት

የሚበጣጥስ መራራ ሐሞት መጠጣት ምን ይደንቅ?

የዚህ ሁሉ ደግነት ምንጩ አምላካዊ ፍቅር መሆኑ ከቶም

አያጠራጥርም!ይህን ሊያደርገው የሚያስብ እንኳ ከሰው

ወገን አይገኝምና። ከነቢያት ወገን በደንጊያ የተወገሩ

በስለት የተቆረጡ ለአራዊት የተጣሉ ነበሩ፤ይህን ሁሉ

መከራ መቀበላቸው ለራሳቸው የሚከብሩበት ዋጋ

የሚያገኙበት ስለሆነ፤አንድም መከራውን

ከመቀበል ሌላ የሚያደርጉት ባይኖራቸው ነው።


ክርስቶስ ግን ሲገርፉት በጦር ሲወጉት ይህን ሁሉ

አስጨናቂ መከራ የተቀበለው የቆሰለው የሞተው

ሕማሙ ሞቱ ለእርሱ የሚያሻው ወይም የሚረባው

ሆኖ መከራውንም ከእርሱ ማራቅ ሳይቻለው ቀርቶ

አይደለም።በገዛ ፈቃዱ ሰው ሆኖ እንደተወለደ መከራ

የተቀበለውና የሞተውም በገዛ ፈቃዱ ነው፤ሰውን

ወዶታልና ታመመለት፣ ቆሰለለት፣ ሞተለት።ወደር

ለሌለው ፍቅሩ ማረጋገጫው የመስቀል ላይ ሞቱ ነው፤

እርሱ ራሱ ጌታ እንደነገረን ራስን ለሞት አሳልፎ ከመስጠት

በላይ ፍቅር የለምና።ዮሐ ፫፥፲፮፣ ፲፭፥፲፫ ፩ ዮሐ ፬፥፲


እሑድ በሌሊት በእስራኤል ወግ መሠረት ሽቱ ይቀቡት

ዘንድ ወደ መቃብሩ የተጓዙ ቅዱሳት አንስት ወደ መቃብሩ

ሲደርሱ የመቃብሩ ግጣም ደንጊያ ተነሥቶ መቃብሩ ባዶ

ሆኖ አገኙ፤ፍርሀት አደረባቸው። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር

መልአክ ተገልጾ “ተንሥአ በከመ ይቤ =እንደተናገረው

ተነሥቷል”በማለት እሞታለሁ በሦስተኛውም ቀን

ከሙታን ተለይቼ እነሣለሁ ብሎ ለሐዋርያት አስቀድሞ

እንደነገራቸው ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ ነገራቸው።

በዚህም የመልአኩ የምስራች ቃል የቅዱሳት አንስት

ኀዘናቸው ተወገደ ፍርሀታቸውም ራቀ። ያዩትንና

የሰሙትንም በአንድ ቤት ውስጥ ተሰባስበው ሲያዝኑ

ሲተክዙ ለነበሩ ደቀመዛሙርቱ ለመንገር እየተቻኮሉ

ሲሄዱ ክብር ይግባውና ጌታ ራሱ ተገለጸላቸው፤ ሰማን

ብቻ ብለው ሳይሆን አየን ብለው እንዲመስክሩ

የምስክርነት ተልእኮ ሰጣቸው። ማቴ ፳፰፥፱


በቅዱስ አንደበቱ “አነ ው እቱ ትንሣኤ ወሕይወት =

ሕይወትና ትንሣኤ እኔ ነኝ”(ዮሐ ፲፩፥፳፭)ብሎ እንደተናገረ

የሰዎችን ትንሣኤ ለማብሰር ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤

የሐዋርያትም አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ጉባኤ

“እስመ ኢይክል ሞት እኂዞቶ == እርሱን ሞት ሊይዘው

አይችልምና” (ሐዋ ፪፥፳፬) ብሎ እንደመሰከረ ሞት

የመለኮትን ኀይል መቋቋም ስላልተቻለው ኀይሉ ተሰበረ፤

የሞት አበጋዝ ዲያብሎስ ሲታሠር የበደል እሥረኛው ሰው

አርነት ወጣ።


የተነሣው እንደ አልዓዛር ያለ መልሶ ሟች አይደለም፤

በባሕርየ መለኮቱ ሞት የሌለበት ሥግው ወልድ ነው

እንጂ። (፩ ጴጥ ፫፥፲፰) የተነሣው በኤልያስ ጸሎት

እንደተነሣው እንደ ዮናስ ያለ የዋህ ብላቴና አይደለም፤

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ

ዘንቃህ እም ንዋም == እግዚአብሔር ከእንቅልፍ

እንደሚነቃ ሰው ተነሣ ብሎ” (መዝ ፸፯፥፷፭) የዘመረለት

ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ እግዚአብሔር ነው እንጂ።

ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ ለአጋንንት ውድቀታቸው

ለእኛ ግን ትንሣኤያችን ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤ

ለአይሁድ ኀዘናቸው ለእኛ ግን ደስታችን ነው።


የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ወገኖች የክርስቶስን

ትንሣኤ ስታከብሩ የራሳችሁን ትንሣኤ እያከበራችሁ

መሆኑን ልታስቡ ይገባል፤ ወድቀን ነበረ አሁን ግን

ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ እየወደቀ እየተነሣ ቀራንዮ

በመውጣቱ ወደ መቃብር በመውረዱ በመጨረሻም

ከመቃብር በመነሣቱ ከውድቀታችን ተነሥተናል፤

ለአጋንንት መገዛት ቀርቶልናል፤ነፃነት የተሰበከልን ነፃ

የመንግሥተ እግዚአብሔር ዜጎች ሆነናል።አሕዛብ ግራ

ቢገባቸውም እኛ ዛሬም የሞተልንን ጌታ በጾም

በጸሎትና በስግደት እናከብረዋለን፤ በትንሣኤውም

ትንሣኤያችንን ላወጀልን አምላክ በሐሴት እንዘምራለን።

 

ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለመቀል

ሞት የተሰጠበትን የፍቅሩንብዛት የሚወዳደር ፍቅርና

ርኅራኄ ባይኖረንም በፍጹም ልባችን እናምነዋለን፤

እንታመንለታን፤መቼም መች ቢሆን የእርሱን ቸርነት

ለአፍታም አንዘነጋውም።የነፃነታችሁ በዓል የክብርና

የልዕልናችሁ ቀን ነውና በመንፈሳዊ ደስታ ደስ ይበላችሁ፤

ልባችሁን በኀዘን አትጣሉ። በዓለም ላይ በሚከሠት

ማንኛውም መከራና ኀዘን አትሸበሩ፤ አምላካችን እኮ

ኀዘናችንን አይወደውም፤ ውድቀታችንንም አይሻውም።

ይህማ ባይሆን ኖሮ ሰው መሆን ባላስፈለገው፤ መራራ

ሐሞት መጠጣትም ባላሻው ነበር።


በርግጥ ሥጋ ከነፍስ ይህም ዓለም ከወዲያኛው ዓለም

ስለማይበልጥ ስለማይሻልም አምላካችን ለወዳጆቹ

ከሥጋችን ይልቅ ለነፍሳችን ከምድራዊ ኑሮአችን ይልቅ

ለሰማያዊ ኖሮአችን ያስብልናል። ይህ ማለት ግን በዚህ

ዓለም ስንኖር ኑሮአችን ሥቃይና ሲቃ ዋይታና ወዮታ

የበዛበት ቢሆንም ግድ አይለውም ማለት አይደለም።

የማርያምና የማርታን እንባ ሊያብስ ወደ አልዓዛር

መቃብር የወረደው ሲያለቅሱም አብሮ ያለቀሰው ደጉ

ቸሩና ርኅሩሁ መድኃኔዓለም እኮ ነው ዛሬ ከሞት ተነሣ

ብለን የምናከብረው፤ ዘወትርም በምልጃና በጸሎት

የምንማፀነው ወይን አልቆባቸው ሰዎች ተጨንቀዋል

ብላ ምታሳስብ ደግና ርኅርኅት እናት ወዳለችው

ደግና ርኅሩኅ ክርስቶስ እኮ ነው! ምንም የዓለም

ክፋቷና ክህደቷ ቢበዛም እርሱ ግን የማይለወጥ

ፍቅር ያለው የፍቅር አምላክ ስለሆነ ዛሬም

እንደሚያዝንን ዛሬም እንደሚራራልን ከወደቅንበት

አዘቅት ሊያወጣን አልዓዛር አልዓዛር ብሎ እንደሚጠራን

በፍጹም ልባችን ልናምን ይገባል።


ወገኖቼ በሰዎች ላይ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤

አምላካችን ግን ተስፋ የሚቆረጥበት አምላክ

አይደለም፤ “አነ እሄሉ ምስሌክሙ በኵሉ መዋዕል

== እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” (ማቴ ፳፰፥፳)

ያለው ቃሉ የታመነ ነው፤ የትንሣኤው ጌታ ዛሬም ከእኛ

ጋር አለ! እርሱን ከእኛ ጋር ሳለም ደዌም ቢሆን

ድርቅም ቢሆን ሌላም መከራ ፈጽሞ እንደማያጠፋን

ልናምን ይገባል።


በአምላኩ ላይ ላመፀ ዓለም ጥቂት ተግሣጽ አይገባም

ማለት አይቻልም፤በምክሩና በፈቃዱ ማንም ጣልቃ

ይገባ ዘንድ አይቻለውም፤ ፍቅሩ ግን አባትነቱ ግን

ስለእኛ እንዲራራ ስለእኛ ምሕረትን እንዲያዝ ግድ

ይለዋልና እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ፤በሚቻለን

ሁሉ ለሰዎች ስለሰዎች መልካም እናድርግ፤ ከክርስቶስ

የቤዛነት ሞት የምንማረው አንዱ ትምህርት ይህ ነውና።

እርሱን ተስፋ እናድርግ፤ ጌታችን ይህን አስጨናቂ ጊዜ

አሻግሮ ዕረፍትና ሰላም ጸጥታና በረከት ካለበት ዘመን

እንደሚያደርሰን እናምናለን።


በድጋሚ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የበረከት በዓል

ይሁንላችሁ፤ለዓለም ሰላምን ይስጥልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  አሜን።

 

Last Updated on Saturday, 18 April 2020 15:20
 
በኢትዮጵያ በወረርሽኙ ለችግር የተዳረጉትን ወገኖች መርዳት ይገባል ተባለ። PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Sunday, 29 March 2020 08:41

ካስል ጀርመን(መጋቢት ፳ - ፳፻፲፪ ዓ.ም) በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት

እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው በሀገራችን ኢትዮጵያ ለችግር

የሚዳረጉ ወገኖቻችንን መርዳት እንደሚገባ ተጠቆመ።


በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአካል የተቋረጠው አገልግሎት በስካይፔና

በዩቲዩብ በዛሬው እለትም በጸሎትና በምህለላ ቀጥሎ ውሏል።


የትንሳኤ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብርሄርን አስመልክተው ትምህርት

የሰጡት የብሬመን ቅዱስእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ

ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም እንዳሉት ወቅታዊው ችግር በምጽአት ቀን

ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለሚነሱት አብዛኞቹ ጥያቄዎች በምድር

መልስ የምንሰጥበት ነው።


ስራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ስታመም አልጎበኛችሁኝም፣

ሳዝን አላጽናናችሁኝም የሚሉት ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በአንድ ላይ

የመጡበት ሁኔታ ተከስቷል ያሉት ቀሲስ ያብባል እግዚአብሔር

ከሰጠን ጸጋ ለወገኖቻችን በማካፈል የነፍስ ሥራ እንድንሰራም አሳስበዋል።


በመላው ዓለም በተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ተቋማትና

የንግድ እንቅስቃሴዎች በመዘጋጀታቸው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ

በሚተዳደሩ ወገኖቻችን ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱ አይቀርም።


በተለይ በሀገራችን በአብነት ትምህርት ቤቶች በአነስተኛና በጥቃቅን የሥራ

ዘርፎች የተሰማሩ ወገኖቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ

የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በተገኘው መንገድ ሁሉ እጃችንን

እንድንዘረጋም ጥሪ አቅርበዋል።


አምላካችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቃሉ “በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ

እሾምሃለሁ“ ማቴ ፳፬፦፳፭ ብሎ እንደተናገረ ካለን ጸጋ ላይ በማካፈል

ምግባር ከሃይማኖት ይዘን ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ

የአምላካችን ፈቃድ እንዲሆንም ተማጽነዋል።


በቀጥታ ስርጭቱ ዛሬም ፻፴ የሚደርሱ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት

ቤተሰቦች ሲካፈሉ የየደብሩ መዘምራን አጥንት የሚያለመልሙና በበገና

የታገዙ መዝሙሮችን አቅርበዋል።


ምእመናኑም ስለ መርሐ ግብሩ በሰጡት አስተያየት ካህናቱና ዲያቆናቱ

ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ አገልግሎቱን ማስቀጠላቸው አሁንም ከቤተ

ክርስቲያን በአካልም በመንፈስም እንዳልራቅን እንዲሰማን

አድርገዋል ብለዋል።ለክህናቱና ለዲያቆናቱም ረጅም የአገልግሎት

እድሜን ተመኝተዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ

ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም የሚመራው የጸሎት የምሕለላና የስብከተ

ወንጌል አገልግሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ

በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል መገናኘት እስኪቻል ድረስ

ሁልጊዜ ረቡእ እና ዓርብ ምሽት ለአንድ ሰዓት ተኩል ዘወትር

እሁድ ደግሞ ማለዳ ለሁለት ሰዓት የቀጥታ ስርጭቱ በማኅበራዊ

መገናኛ ብዙሃኑ ይቀጥላል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

አሜን።

 

Last Updated on Sunday, 29 March 2020 09:17
 
ወቅታዊው ወረርሽኝ የንስሃ ሕይወት ማንቂያ ደወል ነው። PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Wednesday, 25 March 2020 22:10

ካስል ጀርመን(መጋቢት ፲፮- ፳፻፲፪ ዓ.ም) ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለንስሃ ጊዜ አለን ብለን ለተዘናጋን ክርስቲያኖች

የማንቂያ ደውል እንደሚሆን ተጠቆመ።


በአውሮፓ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጠው የሰርክ ጸሎትና ምሕለላ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።


በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቋረጠውን የቤተ ክርስቲያን

አገልግሎት በስካይፔና በዩቲዩብ የማስቀጠሉ አገልግሎት በዛሬው እለትም ተጠናክሮ ቀጥሏል።


በተለይም በዛሬው ምሽት የሰርክ ጸሎትና ምሕለላ አገልግሎት እንደ አገሬው አቆጣጠር ከምሽቱ 19-20፡30 ሰዓት ድረስ በካስል

ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም በሐምቡርግ ደብረ መድሀኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና በብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ አብያተ

ክርስቲያናት የሚገኙ ምእመናን የቀጥታ ስርጭቱ ተሳታፊ ሆነዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም በሚመራው የጸሎት የምሕለላና

የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል መገናኘት እስኪቻል

ድረስ ሁልጊዜ ረቡእ እና ዓርብ ምሽት ለአንድ ሰዓት ተኩል ዘወትር እሁድ ደግሞ ማለዳ ለሁለት ሰዓት የቀጥታ ስርጭቱ

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ ይቀጥላል።


የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም እንዳሉት በዓለማችን

የተከሰተውን ወረርሽኝ እግዚአብሔር እስኪያስወግድልን ድረስ ጸሎታችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል።


እግዚአብሔር ቸርና መሃሪ ነው ያሉት ቀሲስ ያብባል አላዛርን ከሞት ያነሳ አምላክ ከዚህም ወረርሽኝ ይታደገናል።እግዚአብሔር

ሥራውን የሚሰራበት ጊዜ ስላለው ተግተን እንድንጸልይም አስገንዝበዋል።


ከሞት በሁዋላ በክርስቶስ ሕይወት እንዳለ ለምናምን ክርስቲያኖች አሁን በዓለማችን በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ መጨነቅ

የለብንም፤በዚህ ወቅት ከእኛ የሚጠበቀው በእምነታችን ፀንተን ጸሎት ማብዛት ደግነት ማብዛት በጎ ሥራን በማብዛት መረጋጋት

እንደሆነም ነው ያሳሰቡት።


መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ንስሐ ግቡ ሲባል ገና ብዙ ጊዜ አለንስንል ለነበርን ምእመናን ሞት መቼ እንደሚመጣ እንደማይታወቅ

ወቅታዊው ሁኔታ የማንቂያ ደወል በመሆኑ ትንሳኤና ሕይወት የሆነው አምላካችን ከሃዘንና ከመከራ እንደሚያወጣን በማመን ለንስሃ

እንድንዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

 

Last Updated on Wednesday, 25 March 2020 22:24
 
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የስብከተ ወንጌልና የጸሎት አገልግሎቱ ቀጥሏል። PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Sunday, 22 March 2020 11:14

ካስል ጀርመን (መጋቢት ፲፫ - ፳፻፲፪ ዓ.ም)  በአውሮፓ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የስብከተ ወንጌልና የጸሎት አገልግሎቱ

እንደቀጠለ ነው።

 

ዛሬም በኮሮና ወረርሸኙ ምክንያት በየአብያተ ክርስቲያናት መሰባሰብ ባለመቻሉ በጀርመንና አካባቢው

የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከት ካህናት የጸሎት፣ የስብከት፣ የምሕለላና የመዝሙር አገልግሎት

በዩቲዩብና በስካይፔ በቀጥታ ስርጭት አማካኝነት ሲሰጥ አርፍዷል።


በተለይም የካስል ደ/ቀ/ መድኃኔዓለም ፣የሐምቡርግ ደብረ መድሐኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና የብሬመን

ቅዱስ እስጢፋኖስ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በጋራ ባዘጋጁት የዩቲዩብና የስካይፔ ገጽ ተሳታፊ ሆነዋል።


በቀጥታ ስርጭት በተካሄደው መርሐግብርም እስከ ፻፴ የሚደርሱ ቤተሰቦች ተካፍለዋል።


የካስል ደ/ቀ/መድኃኔዓለምና የሐምቡርግ ደብረ መድሀኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት

አስተዳዳሪ መጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስ የአብይ ጾም 5ኛ ሳምንት የደብረዘይትን በዓል

አስመልክተው እንዳስተማሩት በዓሉ የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአቱ

የሚታስብበት ነው።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለደቀመዛሙርቱ የዳግም መምጣቱን ምልክቶችና

ምሥጢሩን ገልጾላቸዋል ያሉት መጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ በነገረ ምጽአቱ እንደተጠቆመው በፍየል

የመሰላቸውን ሃጥአን በግራ በበግ የመሰላቸው ቅዱሳንን ደግሞ በቀኙ ያቆማቸዋል።


በምድር ላይ የጽድቅ ሥራ በመሥራትና የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ የምትለዋን የአምላካችንን ቃል

ለመስማት ብሎም ዘላለማዊ መንግስቱን ለመውረስ ሃይማኖታዊ ግዴታችንን መወጣት እንዳለብንም

አስገንዝበዋል።


“ እናንተ ግን ከሁሉ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እሹ“ የሚለውን የአምላካችንን ቃል

መሰረት በማድረግም የማያልፈውን ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ዘወትር መጸለይ መለመንና ምሕለላ

ማድረግ እንጂ ለተገደበው ለዚህ ዓለም መጨነቅ እንደሌለብንም አስምረውበታል። ሥጋችን በምድር

ብትሆንም ነፍሳችን ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት በር ማንኳኳት እንዳለባትም እንዲሁ።


እግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሾች እንዲያደርገንም ተግተን እንድንጸልይ መክረዋል።


የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል

ሙሉዓለም በበኩላቸውም በዓለማችን የተከሰተውን ወረርሽኝና ደዌያትን እግዚአብሔር እስኪገስጽልን

ድረስ ከአምልኮታችን በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በመቀበል እንድንተገብርም

አሳስበዋል።


ከሦስቱም አብያተክርስቲያናት የተመረጡ መዘምራንም ወቅቱን የሚዋጁ መዝሙሮችን አቅርበዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም

በተመራው የጸሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል

መገናኘት እስኪቻል ድረስ የቀጥታ ስርጭቱ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ እንደሚቀጥል ታውቋል።


ምእመናንም ለዚሁ አገልግሎት ወደተዘጋጀው የዩቲዩብ ቻናል/መስመር/ በመግባት በቀጥታ ተሳታፊ

እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

Last Updated on Sunday, 22 March 2020 12:19
 
« StartPrev12345678910NextEnd »

Page 1 of 12

Who's Online

We have 13 guests online

ሌሎች ድረ ገጾች

Featured Links:

feed-image Feed Entries


Powered by Medhanealem.