Home
Welcome to the Frontpage
የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል በደብራችን በድምቀት ይከበራል። PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Monday, 25 April 2016 05:41

 

ካስል ሚያዝያ /፳፻፰ ዓ.ም (ጀርመን) የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ከበዓለ ስቅለት ጀምሮ የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደሚኖሩ በጀርመን ሀገር የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስታውቋል።

በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በደቡብ፣ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ለምእመናን ባስተላለፈው መልእክት እንዳስታወቀው የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ዘንድሮ በደብሩ ለሦስተኛ ጊዜ ከበዓለ ስቅለት ጀምሮ የስግደት፣ የጸሎት፣ የትምህርትና የቅዳሴ አገልግሎት ይሰጣል።

የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በስደት ሀገር በተቻለ መጠን የተሟላ አገልግሎት ለምእመናኑ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ አጋጣሚ መላው ምእመናንና ምእመናት በሙሉ በበዓሉ ላይ ተገኝተው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በዓል በፍጹም መንፈሳዊ ሥርዓት እንዲያከብሩና ከአምላካችን በረከት እንዲሳተፉም ደብሩ ጥሪውን አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓመታዊው የቅዱስ አምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለት የሚታሰብበት የመድኃኔዓለም በዓል ከደብረ ዘይት በዓል ጋር ተጣምሮ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በደብራችን እጅግ በደመቀ ሁኔታ መከበሩ እንዳስደሰታቸው የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

 

የመድሃኔዓለም ጥንተ ስቅለቱ የሚታሰብበትና የደብረ ዘይት በዓል በጣምራ ሲከበር ከተገኙት አባቶች በከፊል/ፎቶ በአቶ ጣለው ዳመነ/

 

የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የሀገረ ስብከታችን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ በተገኙበት በደብራችን በተከበረው በዓልም ቁጥራቸው በርካታ ምእመናን ከመላው ጀርመን የተገኙ ሲሆን የበዓሉ ድባብ ፍጹም መንፈሳዊና የሀገር ቤቱን ሥርዓት አሟልቶ መከናወኑ የበለጠ ሐሴትን ፈጥሮልናል ነው ያሉት ምእመናኑ።ከዝግጅትና ከመስተንግዶ በተጨማሪ መንፈስን የሚያለመልም መንፈሳዊ ሥርዓት መከናወኑ ለሌሎችም አጥቢያዎች ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ምእመናኑ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል ይኽው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመጠየቅ።

በበዓሉ ላይ የደብሩ ሕንፃ አሰሪ ኮሚቴ አጭር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በዕለቱ የተሰባሰበውን ሳይጨምር ከ50 ሺ ዩሮ በላይ ከምእመናን የቃል ኪዳን ሰነድና ከተለያዩ አገልግሎቶች የተሰባሰበ ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀው የማይንቀሳቀስ ሂሳብ ውስጥ መግባቱም ይፋ ተደርጓል።ምእመናን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል።በዕለቱም ለካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግዢ የሚውል ከ5 ሺ ኦይሮ በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በዚሁ በዓል ላይ በዲያቆንነት ደብራችንን ለረዥም ጊዜ በማገልገል ላይ የሚገኙት ወንድማችን ዲያቆን (አሁን ቀሲስ) ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም በደብራችን አስተዳዳሪና በአገረ ስብከታችን ዋና ፀሐፊ በመጋቤ ምስጢር ኀሩይ ኤርምያስ አቅራቢነት የቅስና ማዕረግ ተቀብለዋል።

 

 

ወንድማችን ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም የቅስና ማዕረግ ሲቀበሉና ከሊቀጳጳሳችን ከብጹዕ አቡነ ሙሴ እጅ መስቀል ሲበረከትላቸው/ፎቶ በመስፍን አብርሃ/

ቀሲስ ዶክተር ያብባል በአገር ቤት የሚገኙ ገዳማትን አብያተ ክርስቲያናትና ድጋፍ የሚሹ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኙ ትሁትና ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ዕውቀታቸውንና ሀብታቸውን ጭምር የሚያበረክቱ አባት ናቸው።

ገቢው ለሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት ማጠናከሪያ እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀው ቶምቦላ ዕጣም በዕለቱ ወጥቷል ።በዚህም መሰረት የኢየሩሳሌም ደርሶ መልስ የአየር ትኬት ከሳምንት የሆቴል ቆይታ ጋር የሚያድለው 1ኛ ዕጣ 000538፤ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር የሚያስገኘው 2ኛ ዕጣ 002127፤ ብስክሌት የሚያስገኘው 3ኛ ዕጣ 000141፤ ታብሌት ኮምፒዩተር የሚያስገኘው 4ኛ ዕጣ 000529፤ 5 የሰዓታት መጽሓፍት ከነ ሲዲ የሚያስገኘው 5ኛ ዕጣ 002102፤ 25 ልዩ ልዩ ሽልማቶችን የሚያስገኘው 6ኛ ዕጣም 001712 በመሆን ወጥቷል።

ዕድለኛ ምእመናንም የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት በማነጋገር ሽልማታቸውን እንዲረከቡ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

 

 

 

Last Updated on Monday, 25 April 2016 07:41
 
ተንሥእ፡ እግዚኦ፡ ርድአነ፤ ወአድኅነነ፡ በእንተ፡ ስምከ! PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Monday, 20 April 2015 08:37

ተንሥእ፡ እግዚኦ፡ ርድአነ፤ ወአድኅነነ፡ በእንተ፡ ስምከ!


ከሁለት ወራት በፊት በሊብያ ምድር በ21 የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ላይ አይሲስ በተባለው የጥፋት መልእክተኛ አክራሪ እስላማዊ ቡድን በግፍ የተፈጸመባቸውን ጭፍጨፋ ከሰማንበትና ቡድኑ ወንጀሉን እንደ መልካም ገድል ነውሩን እንደ ጽድቅ ሥራ በመቁጠር ዓለም እንዲያይለት በአየር ላይ ያዋለውን ምስል ካየንበት ጊዜ ጀምሮ ልባችን በኀዘን ሲቃትት አእምሮአችን ሲታወክ በምሕላና በጸሎት ሰንብተን ኀዘኑ ገና ከልባችን አልወጣም። ትናንትና እሑድ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ይኸው አረመኔያዊ ግፍና ወንጀል በ28 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል።

የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገራቸው ወጥተው ከሀገር ወደ ሀገር ሲንከራተቱ የነበሩ እነዚሁ ወገኖች ዘግናኝ የሆነው ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ክርስቲያን ሆነው በመገኘታቸውና እስልምናን በኃይል እንዲቀበሉ ተጠይቀው ሃይማኖታቸውን ክደው እስልምናን መቀበል ባለመፈለጋቸው መሆኑን የአክራሪ ቡድኑን የቪድዮ መልእክት ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ሚድያዎች አስታውቀዋል።

እንደ ግብጻውያን ወንድሞቻችን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን በአክራሪ ሰይፍ ሲቀሉ ደማቸው እንደ በግ ደም ሲፈስ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲቃጠል ይህ የመጀመሪያ አይደለም፤ በገዛ ሀገራቸው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የተሠዉት፣ በእሳት የተቃጠሉት፣ በሳዑዲ ዐረቢያ በየአድባባዩ እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው አስከሬናቸው መንገድ ለመንገድ የተጎተተው፣ የፈላ ውኃ የተደፋባቸው ኩላሊት የተነጠቁት፤ በደቡብ አፍሪካና በየመንም ሰሞኑን አሰቃቂ መከራ የደረሰባቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም።

Last Updated on Monday, 20 April 2015 08:48
Read more...
 
ሰሙነ ሕማማት PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Tuesday, 07 April 2015 20:59

ሰሙነ ሕማማት

በመምህር ጌቱ መንክር

ሰሙነ ሕማማት የሚለው የጊዜ ስያሜ ሰሙን እና ሕማማት የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ሰሙን ስምንት፣ ሳምንት ፤ ሕማም ወይም በብዙ ሕማማት ማለት ደግሞ በቁሙ ሕመም ሕመሞች ፣ መከራ፣ እንግልት ማለት ነው። በጥቅሉ ሰሙነ ሕማማት ማለት የሕማም የመከራ ሳምንት ማለት ነው።  ሳምንቱ በዚህ ስያሜ የተጠራው ጌታ መዋዕለ ስብከቱን ሲፈጽም በለበሰው ሥጋ ብዙ ጸዋትወ መከራ የተቀበለበት ሳምንት በመሆኑ ነው። መከራ የተቀበለው በርግጥ ከኀሙስ ሌሊት ጀምሮ ቢሆንም በመጋቢት ፳፪ ቀን እሑድ“ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት“፤ “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር“ በሚል የዐዋቆችና የሕፃናት ምስጋና ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ በኋላ አይሁድ በየዕለቱ የሚከሰስበትን የሚፈረድበትን በሞት የሚቀጣበትንም ምክንያት ሲፈልጉ፣ ሲመክሩና ይሙት በቃ ሊያስፈርዱበት ሲስማሙ ሲያስማሙ በመሰንበታቸው ሳምንቱ ሁሉ ጌታ ቡሩክ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ስለማዳን በገዛ ፈቃዱ የተቀበላቸው መከራዎቹ የሚታሰቡበት ልዩ የጸሎት፣ የስግደትና የሱባዔ ሳምንት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ይባላል።

Last Updated on Tuesday, 07 April 2015 21:11
Read more...
 
የሐዘን መግለጫ PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Thursday, 19 February 2015 20:55

የሐዘን መግለጫ

“ነገር ግን ሰዓት ትመጣለች እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርብ ይመስለዋል“

ዮሐ ፲፮፥፪

በዕለተ ሰንበት በሊብያ ምድር በሃያ አንድ ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን ላይ አይሲስ ተብሎ በሚታወቀው የአክራሪ እስልምና ሚሊሻዎች የተፈጸመውና ሰሞኑን የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ የሆነው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ነው ይህን ቃል እንድናስታውሰው ያደረገን። በርግጥ ለግብጽ ምእመናን መታረድ፣ መታሠርና መቃጠል አዲስ ነገር አይደለም፤ ክርስትናን በልብና በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሥጋቸው እጅግ የሚዘገንኑ መከራዎችን በመቀበል ሲኖሩት ዓለምም ከንፈር ሲመጥላቸው ከ1 ሺህ አምስት መቶ ዓመት በላይ አስቆጠረዋል? አይሲስ የተባለው አዲስ በቀል አክራሪ ቡድን ከዚህ በፊት በሶርያና በኢራቅ በክርስቲያንና ባላከረሩ የእስልምና ተከታዮች ላይ ተመሳሳይ ምናልባትም የከፋ ግፍ ሲፈጽም መቆየቱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ወደሌሎች አካባቢዎች የእንቅስቃሴ አድማሱን በማስፋት በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጽመው ኢሰብአዊ ጭፍጨፋና አፈና የጥፋት ተልእኮው ተጠናክሮ መቀጠሉንና ያልተረዱ ሰዎች እግዚአብሔርን ያገለገሉ እየመሰላቸው የገዛ ወገኖቻቸውን እንደ በግ የማረዱን ተግባር ማደላደላቸውን የሚያመላክት ነው።

 

ዓለም ወዴት እያመራች ነው? ከርስቲያን ወገኖች እስከ መቼ ድረስ ይሆን ሳይገፉ እየተገፉ፤ ሳይበድሉ እየተበደሉ የሚኖሩት? በግፍ የሚታረዱ ወገኖችን የሚደርስላቸው ማን ይሆን? ዓለም ለክርስቲያኖች ምንም ቦታ የላትምን? ለማንኛውም እንዲህ ያለውን መከራ በጾምና በጸሎት ስለሆነ ሊዋጉት የሚገባው የዝግጅት ክፍላችን አምላክ የጥፋት መልእክተኞቹን ኃይል እንዲሽርልን የምእመናንም ስደትና እልቂት እንዲያስቆምልን በርትተን እንጸልይ የተሠዉት ወገኖቻችንና ለመከራ የተጋለጡትን ሁሉ በጸሎታችን እናስባቸው በማለት መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፤ ለግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ለተከታዮቿ በሙሉ መጽናናትንም ይመኛል።ወስብሃት ለእግዚአብሔር

በአይሲስ አንገታቸው የተቀላው ግብፃውያን ሰማዕታት በከፊል


 

Last Updated on Thursday, 19 February 2015 21:16
 
« StartPrev12345678910NextEnd »

Page 3 of 12

Who's Online

We have 18 guests online

ሌሎች ድረ ገጾች

Featured Links:

feed-image Feed Entries


Powered by Medhanealem.