Home Category Blog ሰሙነ ሕማማት
ሰሙነ ሕማማት PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Tuesday, 07 April 2015 20:59

ሰሙነ ሕማማት

በመምህር ጌቱ መንክር

ሰሙነ ሕማማት የሚለው የጊዜ ስያሜ ሰሙን እና ሕማማት የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ሰሙን ስምንት፣ ሳምንት ፤ ሕማም ወይም በብዙ ሕማማት ማለት ደግሞ በቁሙ ሕመም ሕመሞች ፣ መከራ፣ እንግልት ማለት ነው። በጥቅሉ ሰሙነ ሕማማት ማለት የሕማም የመከራ ሳምንት ማለት ነው።  ሳምንቱ በዚህ ስያሜ የተጠራው ጌታ መዋዕለ ስብከቱን ሲፈጽም በለበሰው ሥጋ ብዙ ጸዋትወ መከራ የተቀበለበት ሳምንት በመሆኑ ነው። መከራ የተቀበለው በርግጥ ከኀሙስ ሌሊት ጀምሮ ቢሆንም በመጋቢት ፳፪ ቀን እሑድ“ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት“፤ “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር“ በሚል የዐዋቆችና የሕፃናት ምስጋና ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ በኋላ አይሁድ በየዕለቱ የሚከሰስበትን የሚፈረድበትን በሞት የሚቀጣበትንም ምክንያት ሲፈልጉ፣ ሲመክሩና ይሙት በቃ ሊያስፈርዱበት ሲስማሙ ሲያስማሙ በመሰንበታቸው ሳምንቱ ሁሉ ጌታ ቡሩክ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ስለማዳን በገዛ ፈቃዱ የተቀበላቸው መከራዎቹ የሚታሰቡበት ልዩ የጸሎት፣ የስግደትና የሱባዔ ሳምንት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ይባላል።

 

ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም ጋር የተያያዘ የሱባዔ ጊዜ ከሆሣዕና ማግሥት እስከ ትንሣኤ ዋዜማ ያሉትን  ስድስት ቀናት የሚያጠቃልል ዕለታቱ የየራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው።

ሰኞ፦ ማለትም ሰውን አስረግማ የተረገመችው ዕፀ በለስ ለመጨረሻ ጊዜ የተረገመችበት የርግማን ዕለት ነው። ማቴ ፳፩፥፲፰ ማር ፲፩፥፲፪

ማክሰኞ፥ በማን ሥልጣን ይሄን ታደርጋለህ ብለው የጠየቁበት ዕለት። ማቴ ፳፩፥፳፫ ላይ ወደመቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደእርሱ ቀረቡና በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? ብለው ጠየቁት። ጌታችን የመለሰላቸውን መልስ በዚሁ ምዕራፍ ላይ መመልከት ይቻላል።

ረቡዕ፦ የጌታችን የመድኃኒታችን ምክረ ሞት የተፈጸመበት ዕለት ነው። “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነው። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኮል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይመክሩ ነበር የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሆንም ነበርና።

ኀሙስ፦ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመዋዕለ ስብከቱን የመጨረሻ ትምህርት ያስተማረበት ቀን ነው። ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕፅበተ እግር በመባል ይታወቃል። ደቀመዛሙርቱንም ያጽናናበት ጊዜ ስለነበረች የማጽናናት ዕለት ትባላለች ዮሐ ፲፬፥ ፬-፲፮። በዚህች ዕለት ምሽትም ከራት በኋላ በጌቴሴማኒ ሥርዓተ ጸሎት ፈጽሞ አብነቱን አስተምሮናል። ማቴ ፳፮፥፴፮።

ዓርብ፦ የተመረጠች የመዳን ዕለት ትባላለች። ኀሙስ በነጋው ዓርብ ከቀኑ ፮ ሰዓት ሲሆን ጎልጎታ በተባለው ቦታ ላይ ሰቀሉት ማቴ ፳፯፥፴፫። ጌታችንም በተሰቀለ ጊዜ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብት ከብርሃናቸው ተለይተው ጠፍተዋል። ሉቃ ፳፫፥፵፬ ጌታችንም ፱ ሰዓት ሲሆን በመስቀሉ ላይ እንዳለ ነፍሱን ከሥጋው ለይቷል። ሉቃ ፳፫፥፵፮ ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ መለኮቱ ከሥጋና ከነፍስ አልተለየምና በአካል ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ ነፃነትን ሰብኮ ነፍሳተ ጻድቃንን ወደገነት አስገብቷል። (፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰) ስለዚህ በሥጋ ሞቶ ሳለ በመለኮት ሕያው ነው ብለን እናምናለንል። ከሞተም በኋላ ከጭፍሮቹ አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር በወጋው ጊዜ ደሙ የሕይወት መጠጥ ውሃው የልጅነት ጥምቀት ለመሆን ትኩስ ደምና ጥሩ ውሃ እንደ ለ ፊደል ሆኖ ከጎኑ ወጥቷል። በመሆኑም ዓርብ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ተግባሩ የተፈጸመባት ዕለት ናት።

ቅዳሜ፦ ቅዳሜ ፶፭ኛዋ ቀን ወይም የሱባዔው የመጨረሻ ዕለት ናት። ይህኑ ዕለት ጌታ በመቃብር የዋለባት ዕለት ናት።

በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ሳምንቱ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ሆነን ዘመነ ብሉይን የምናስብበት በመሆኑ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሥርዓተ ፍትሐት፣ ሥርዓተ ቁርባን (ከኀሙስ በስተቀር)፣ ሥርዓተ ጥምቀት (ዘልደት) የሚባሉ የምሥጢር ሥርዓታት/ ምሥጢራት አይፈጸሙም። ምክንያቱም ይህ ወቅት የብሉይ ኪዳን ዘመን የሚታሰብባቸው እንደመሆኑ በብሉይ ኪዳን ነጻነት ስለተገፈፈ ልጅነት ስለተቀማ እነዚህ ሁሉ ሥርዓቶች አይፈጸሙም።

ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላትም እንዲሁ አይከበሩም፤ በዓል የሚከበረው በመንፈሳዊ ደስታ ሱባዔ በተለይም ደግሞ የጌታ ጸዋትወ መከራ የሚታሰብበት ሳምንት የሚገለገለው በስግደትና በምሕላ ነውና። ስለዚህም በዓለ መድኃኔዓለምም በዓለ ማርያምም ቢሆን አልያም የመላእክት የጻድቃን የሰማዕታት በዓል ቢሆን ከሰሙነ ሕማማት ውጪ ይከበራሉ እንጂ ከእነዚህ በዓላት አከባበር  የተነሳ በሰሙነ ሕማማት የሚደረጉ ሥርዓቶች አይቀሩም አይታጎሉም።

በተጨማሪ ፶፭ የሰባዔ ዕለታት ያሉት ዐቢይ ጾም በጠቅላላው የ፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ ምሳሌ ነው፤ ይህም የአዳምና የልጆቹ የሱባዔ ዘመን ነው። ሰሙነ ሕማማትም ለብቻ በራሱ ነፍሳት በሞት ፃዕረኝነት በግብርናተ ዲያብሎስ ተይዘው በኀዘን ላሳለፉት ዓመት ፍዳ ምሳሌ ሲሆን በአዳምና ልጆቹ በዚህ ሁሉ ዘመን የሠሩት በደል በ፴፬ ዓመተ ምሕረት ላይ በፈሰሰው በክርስቶስ ክቡር ደም ተደምስሷል፤ እኛም የእነርሱ ልጆች ነንና የሠራናቸውን የበደል ሥራ ሁሉ ይደመስስልን ዘንድ ጌታ ስለኛ ብሎ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ እያሰብን ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን ፶፭ ቀን እንጾማለን፣ እንሰግዳለን፣ ስለነፍሳችን ድኅነት ወደ ፈጣሪ እንማለላለን።

በሞቱ ላዳነን ለአምላካችን ክብርና ምስጋና ይሁን፣ ሱባዔያችንን ተቀብሎ ቸርነቱን ያድለን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Last Updated on Tuesday, 07 April 2015 21:11
 

ሌሎች ድረ ገጾች

Featured Links:Powered by Medhanealem.