Home የደብሩ አስተዳዳሪ መልእክት ተንሥእ፡ እግዚኦ፡ ርድአነ፤ ወአድኅነነ፡ በእንተ፡ ስምከ!
ተንሥእ፡ እግዚኦ፡ ርድአነ፤ ወአድኅነነ፡ በእንተ፡ ስምከ! PDF Print E-mail
Monday, 20 April 2015 08:37

ተንሥእ፡ እግዚኦ፡ ርድአነ፤ ወአድኅነነ፡ በእንተ፡ ስምከ!


ከሁለት ወራት በፊት በሊብያ ምድር በ21 የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ላይ አይሲስ በተባለው የጥፋት መልእክተኛ አክራሪ እስላማዊ ቡድን በግፍ የተፈጸመባቸውን ጭፍጨፋ ከሰማንበትና ቡድኑ ወንጀሉን እንደ መልካም ገድል ነውሩን እንደ ጽድቅ ሥራ በመቁጠር ዓለም እንዲያይለት በአየር ላይ ያዋለውን ምስል ካየንበት ጊዜ ጀምሮ ልባችን በኀዘን ሲቃትት አእምሮአችን ሲታወክ በምሕላና በጸሎት ሰንብተን ኀዘኑ ገና ከልባችን አልወጣም። ትናንትና እሑድ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ይኸው አረመኔያዊ ግፍና ወንጀል በ28 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል።

የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገራቸው ወጥተው ከሀገር ወደ ሀገር ሲንከራተቱ የነበሩ እነዚሁ ወገኖች ዘግናኝ የሆነው ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ክርስቲያን ሆነው በመገኘታቸውና እስልምናን በኃይል እንዲቀበሉ ተጠይቀው ሃይማኖታቸውን ክደው እስልምናን መቀበል ባለመፈለጋቸው መሆኑን የአክራሪ ቡድኑን የቪድዮ መልእክት ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ሚድያዎች አስታውቀዋል።

እንደ ግብጻውያን ወንድሞቻችን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን በአክራሪ ሰይፍ ሲቀሉ ደማቸው እንደ በግ ደም ሲፈስ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲቃጠል ይህ የመጀመሪያ አይደለም፤ በገዛ ሀገራቸው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የተሠዉት፣ በእሳት የተቃጠሉት፣ በሳዑዲ ዐረቢያ በየአድባባዩ እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው አስከሬናቸው መንገድ ለመንገድ የተጎተተው፣ የፈላ ውኃ የተደፋባቸው ኩላሊት የተነጠቁት፤ በደቡብ አፍሪካና በየመንም ሰሞኑን አሰቃቂ መከራ የደረሰባቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም።

 

ይህ መከራ መቼ ይሆን የሚቆመው? ሃይማኖት በርግጥ ስለ እዚአብሔር መከራ መቀበል እንጂ ሰዎችን ማሳደድ መገድልና ማሠቃየት አይደለምና በሃይማኖት ምክንያት የሞቱትም የተቃጠሉትም ሁሉ የሰማዕታትነት አክሊል የተቀዳጁ ሰማዕታት መሆናቸውን እናምናለን፤ መከራ የተቀበሉለት ጌታ በሰማያዊ መንግሥቱ እንደሚያከብራቸውም እናምናለን። በግፍ ስለፈሰሰው ደማቸው ግን በምሬት እናነባለን፤ እናለቅሳለን፤ ልባችን ሙሾ ያሟሻል፣ ዓይኖቻችን እንባን ያፈሳሉ፤ በአራጆቻቸው እጅ ተይዘው ሞታቸውን እያዩ ከርተት ያሉ ዓይኖቻቸው መቼም ቢሆን ከዓይነ ኅሊናችን ሊጠፋ አይችልም፤ ዓለም ሕግ የላትምን? ዓለም ፍትሕ የላትምን? ዳቦ ያለ በሰይፍ ሲታረድ፣ እንጀራ ብሎ የወጣ በአሸዋ ውስጥ ሲዳፈን መልስ የላትም? ድምጽ የላትም? አንድ ቦንብ አጩሆ የማያውቅ ጨዋና ወንጀል የሚጸየፍ ገራገሩ ኢትዮጵያዊ እዚህም እዚያም ሲወድቅ ምነው አይባልም? ዛሬ በእጃቸው ላይ ጠጠር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ገዳዮቹ እድል ቢገጥማቸው ሚሳኤል ያላቸው አሜሪካውያንንና አውሮፓውያን አይደገምም ይሆን? ታድያ እንደምን በኢትዮጵያውያን ላይ በግፍ የደረሰው ታሪክ የማይረሳው ዘመን የማይሽረው ዘግናኝ ግፍና ጭፍጨፋ እንደምን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሊያውም በምእመናን ላይ ብቻ የታዘዘ መቅሠፍት ሆኖ በቸልታ ይታለፋል? በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል ሆኖ ሊቆጠርና ሰብአዊ አስተሳሰብ ያለው ፍጥረት ሁሉ ሊጯጯህበት የሚገባ ከዚህ የከፋ አደጋ ሌላ ምን ሊኖር ይችል ይሆን?

እንግዲህስ እግዚአብሔር ካልፈረደልን በቀር ሰዎች ምን ቢሉን እንጽናና ይሆን? “ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ መጽናናትንም እንቢ አለች ልጆችዋ የሉምና“ የተባለውና ከ3 ሺህ ዓመት በፊት የተፈጸመው መራራ ግፍና ኀዘን ዛሬ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ምእመናን ላይ ደርሷልና።

ለምእመናንና ለቤተ ክርስቲያኒቱ መጽናናትን እንመኛለን፤ አምላከ ቅዱሳን የሰማዕታቱን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር እንዲደምርልን እንጸልያን፣ አቤቱታችንንም ለፍትሕ አካላት ከማሰማት ወደኋላ አንልም። ምእመናንም በያላችሁበት በግልም፣ በቤተሰብም በማኅበርም ስለደረሰብን መከራ እንድትጸልዩ፣ ወደ ሰማይ አምላክ አቤት እንድትሉ እንማፀናለን።

አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤

ለያዕቆብ መድኃኒትን ያዘዝህ፤

በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፤

በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን፤

በቀስቴ የምታመን አይደለሁም፤

ጦሬም አያድነኝም፤

አንተ ግን ከከበቡን አዳንኸን፤

የሚጠሉንንም ሁሉ አሳፈርሀቸው፤

ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፤

ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን፤ አሁን ግን ጣልኸን አሳፈርኸንም፤

አምላካችን ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም፤

በጠላቶቻችን ዘንድ ወደ ኋላችን መለስኸን፤

ጠላቶቻችንም ተነጣጠቁን፤ እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፤

ወደ አሕዛብም በተንኸን፤

ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፤

ለእልልታችንም ብዛት የለውም፤

ለጎረቤቶቻችን ስድብ፤

በዙርያችንም ሁሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን፤

ለአሕዛብ ተረት፤

ለሕዝቡም የራስ መነቅነቂያ አደረግኸን፤

ዕፍረቴ ሁልጊዜ በፊቴ ነው፤

እፍረት ፊቴን ሸፈነኝ፤

ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፤

ከሚከብብ ጠላት ፊት የተነሣ ነው፤

ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፤

አልረሳንህም ኪዳንህም አላፈረሰንም፤

ልባችንም ወደ ኋላው አልተመለሰም፤

ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፤

በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፤

የሞት ጥላም ሰውሮናልና፤

የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፤

እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፤

እግዚአብሔር ይህን በተመራመረው ነበር!

እርሱ ልባችን የሰወረውን ያውቃልና፤

ስለእርሱ ሁልጊዜ ይገድሉናልና፤

እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል፤

አቤቱ ንቃ ለምንስ ትተኛለህ?

ተነሥ ለዘወትርም አትጣለን፤

ለምንስ ፊትህን ከእኛ ትመልሳለህ?

መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ?

ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጎሳቁላለችና፤

ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና፤

አቤቱ ተነሥ ርዳን! ስለ ስምህም ተቤዠን!

መዝ ፵፫፥፬ ፳፮

 

 

ሌሎች ድረ ገጾች

Featured Links:Powered by Medhanealem.