Home ዜና
ዜናዎች
በኢትዮጵያ በወረርሽኙ ለችግር የተዳረጉትን ወገኖች መርዳት ይገባል ተባለ። PDF Print E-mail
Sunday, 29 March 2020 08:41

ካስል ጀርመን(መጋቢት ፳ - ፳፻፲፪ ዓ.ም) በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት

እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው በሀገራችን ኢትዮጵያ ለችግር

የሚዳረጉ ወገኖቻችንን መርዳት እንደሚገባ ተጠቆመ።


በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአካል የተቋረጠው አገልግሎት በስካይፔና

በዩቲዩብ በዛሬው እለትም በጸሎትና በምህለላ ቀጥሎ ውሏል።


የትንሳኤ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብርሄርን አስመልክተው ትምህርት

የሰጡት የብሬመን ቅዱስእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ

ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም እንዳሉት ወቅታዊው ችግር በምጽአት ቀን

ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለሚነሱት አብዛኞቹ ጥያቄዎች በምድር

መልስ የምንሰጥበት ነው።


ስራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ስታመም አልጎበኛችሁኝም፣

ሳዝን አላጽናናችሁኝም የሚሉት ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በአንድ ላይ

የመጡበት ሁኔታ ተከስቷል ያሉት ቀሲስ ያብባል እግዚአብሔር

ከሰጠን ጸጋ ለወገኖቻችን በማካፈል የነፍስ ሥራ እንድንሰራም አሳስበዋል።


በመላው ዓለም በተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ተቋማትና

የንግድ እንቅስቃሴዎች በመዘጋጀታቸው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ

በሚተዳደሩ ወገኖቻችን ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱ አይቀርም።


በተለይ በሀገራችን በአብነት ትምህርት ቤቶች በአነስተኛና በጥቃቅን የሥራ

ዘርፎች የተሰማሩ ወገኖቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ

የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በተገኘው መንገድ ሁሉ እጃችንን

እንድንዘረጋም ጥሪ አቅርበዋል።


አምላካችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቃሉ “በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ

እሾምሃለሁ“ ማቴ ፳፬፦፳፭ ብሎ እንደተናገረ ካለን ጸጋ ላይ በማካፈል

ምግባር ከሃይማኖት ይዘን ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ

የአምላካችን ፈቃድ እንዲሆንም ተማጽነዋል።


በቀጥታ ስርጭቱ ዛሬም ፻፴ የሚደርሱ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት

ቤተሰቦች ሲካፈሉ የየደብሩ መዘምራን አጥንት የሚያለመልሙና በበገና

የታገዙ መዝሙሮችን አቅርበዋል።


ምእመናኑም ስለ መርሐ ግብሩ በሰጡት አስተያየት ካህናቱና ዲያቆናቱ

ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ አገልግሎቱን ማስቀጠላቸው አሁንም ከቤተ

ክርስቲያን በአካልም በመንፈስም እንዳልራቅን እንዲሰማን

አድርገዋል ብለዋል።ለክህናቱና ለዲያቆናቱም ረጅም የአገልግሎት

እድሜን ተመኝተዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ

ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም የሚመራው የጸሎት የምሕለላና የስብከተ

ወንጌል አገልግሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ

በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል መገናኘት እስኪቻል ድረስ

ሁልጊዜ ረቡእ እና ዓርብ ምሽት ለአንድ ሰዓት ተኩል ዘወትር

እሁድ ደግሞ ማለዳ ለሁለት ሰዓት የቀጥታ ስርጭቱ በማኅበራዊ

መገናኛ ብዙሃኑ ይቀጥላል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

አሜን።

 

 
ወቅታዊው ወረርሽኝ የንስሃ ሕይወት ማንቂያ ደወል ነው። PDF Print E-mail
Wednesday, 25 March 2020 22:10

ካስል ጀርመን(መጋቢት ፲፮- ፳፻፲፪ ዓ.ም) ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለንስሃ ጊዜ አለን ብለን ለተዘናጋን ክርስቲያኖች

የማንቂያ ደውል እንደሚሆን ተጠቆመ።


በአውሮፓ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጠው የሰርክ ጸሎትና ምሕለላ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።


በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቋረጠውን የቤተ ክርስቲያን

አገልግሎት በስካይፔና በዩቲዩብ የማስቀጠሉ አገልግሎት በዛሬው እለትም ተጠናክሮ ቀጥሏል።


በተለይም በዛሬው ምሽት የሰርክ ጸሎትና ምሕለላ አገልግሎት እንደ አገሬው አቆጣጠር ከምሽቱ 19-20፡30 ሰዓት ድረስ በካስል

ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም በሐምቡርግ ደብረ መድሀኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና በብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ አብያተ

ክርስቲያናት የሚገኙ ምእመናን የቀጥታ ስርጭቱ ተሳታፊ ሆነዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም በሚመራው የጸሎት የምሕለላና

የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል መገናኘት እስኪቻል

ድረስ ሁልጊዜ ረቡእ እና ዓርብ ምሽት ለአንድ ሰዓት ተኩል ዘወትር እሁድ ደግሞ ማለዳ ለሁለት ሰዓት የቀጥታ ስርጭቱ

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ ይቀጥላል።


የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም እንዳሉት በዓለማችን

የተከሰተውን ወረርሽኝ እግዚአብሔር እስኪያስወግድልን ድረስ ጸሎታችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል።


እግዚአብሔር ቸርና መሃሪ ነው ያሉት ቀሲስ ያብባል አላዛርን ከሞት ያነሳ አምላክ ከዚህም ወረርሽኝ ይታደገናል።እግዚአብሔር

ሥራውን የሚሰራበት ጊዜ ስላለው ተግተን እንድንጸልይም አስገንዝበዋል።


ከሞት በሁዋላ በክርስቶስ ሕይወት እንዳለ ለምናምን ክርስቲያኖች አሁን በዓለማችን በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ መጨነቅ

የለብንም፤በዚህ ወቅት ከእኛ የሚጠበቀው በእምነታችን ፀንተን ጸሎት ማብዛት ደግነት ማብዛት በጎ ሥራን በማብዛት መረጋጋት

እንደሆነም ነው ያሳሰቡት።


መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ንስሐ ግቡ ሲባል ገና ብዙ ጊዜ አለንስንል ለነበርን ምእመናን ሞት መቼ እንደሚመጣ እንደማይታወቅ

ወቅታዊው ሁኔታ የማንቂያ ደወል በመሆኑ ትንሳኤና ሕይወት የሆነው አምላካችን ከሃዘንና ከመከራ እንደሚያወጣን በማመን ለንስሃ

እንድንዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

 

 
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የስብከተ ወንጌልና የጸሎት አገልግሎቱ ቀጥሏል። PDF Print E-mail
Sunday, 22 March 2020 11:14

ካስል ጀርመን (መጋቢት ፲፫ - ፳፻፲፪ ዓ.ም)  በአውሮፓ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የስብከተ ወንጌልና የጸሎት አገልግሎቱ

እንደቀጠለ ነው።

 

ዛሬም በኮሮና ወረርሸኙ ምክንያት በየአብያተ ክርስቲያናት መሰባሰብ ባለመቻሉ በጀርመንና አካባቢው

የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከት ካህናት የጸሎት፣ የስብከት፣ የምሕለላና የመዝሙር አገልግሎት

በዩቲዩብና በስካይፔ በቀጥታ ስርጭት አማካኝነት ሲሰጥ አርፍዷል።


በተለይም የካስል ደ/ቀ/ መድኃኔዓለም ፣የሐምቡርግ ደብረ መድሐኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና የብሬመን

ቅዱስ እስጢፋኖስ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በጋራ ባዘጋጁት የዩቲዩብና የስካይፔ ገጽ ተሳታፊ ሆነዋል።


በቀጥታ ስርጭት በተካሄደው መርሐግብርም እስከ ፻፴ የሚደርሱ ቤተሰቦች ተካፍለዋል።


የካስል ደ/ቀ/መድኃኔዓለምና የሐምቡርግ ደብረ መድሀኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት

አስተዳዳሪ መጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስ የአብይ ጾም 5ኛ ሳምንት የደብረዘይትን በዓል

አስመልክተው እንዳስተማሩት በዓሉ የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአቱ

የሚታስብበት ነው።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለደቀመዛሙርቱ የዳግም መምጣቱን ምልክቶችና

ምሥጢሩን ገልጾላቸዋል ያሉት መጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ በነገረ ምጽአቱ እንደተጠቆመው በፍየል

የመሰላቸውን ሃጥአን በግራ በበግ የመሰላቸው ቅዱሳንን ደግሞ በቀኙ ያቆማቸዋል።


በምድር ላይ የጽድቅ ሥራ በመሥራትና የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ የምትለዋን የአምላካችንን ቃል

ለመስማት ብሎም ዘላለማዊ መንግስቱን ለመውረስ ሃይማኖታዊ ግዴታችንን መወጣት እንዳለብንም

አስገንዝበዋል።


“ እናንተ ግን ከሁሉ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እሹ“ የሚለውን የአምላካችንን ቃል

መሰረት በማድረግም የማያልፈውን ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ዘወትር መጸለይ መለመንና ምሕለላ

ማድረግ እንጂ ለተገደበው ለዚህ ዓለም መጨነቅ እንደሌለብንም አስምረውበታል። ሥጋችን በምድር

ብትሆንም ነፍሳችን ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት በር ማንኳኳት እንዳለባትም እንዲሁ።


እግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሾች እንዲያደርገንም ተግተን እንድንጸልይ መክረዋል።


የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል

ሙሉዓለም በበኩላቸውም በዓለማችን የተከሰተውን ወረርሽኝና ደዌያትን እግዚአብሔር እስኪገስጽልን

ድረስ ከአምልኮታችን በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በመቀበል እንድንተገብርም

አሳስበዋል።


ከሦስቱም አብያተክርስቲያናት የተመረጡ መዘምራንም ወቅቱን የሚዋጁ መዝሙሮችን አቅርበዋል።


በመጋቤ ምሥጢር ዶክተር ኅሩይ ኤርምያስና በመልአከ ሣህል ቀሲስ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም

በተመራው የጸሎት መርሐግብር አምላካችን ምሕረቱን አውርዶ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአካል

መገናኘት እስኪቻል ድረስ የቀጥታ ስርጭቱ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ እንደሚቀጥል ታውቋል።


ምእመናንም ለዚሁ አገልግሎት ወደተዘጋጀው የዩቲዩብ ቻናል/መስመር/ በመግባት በቀጥታ ተሳታፊ

እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

 
በአውሮፓ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የቤተ ክርስትያን ኣገልግሎት እንዳይቋረጥ ጥረት እየተደረገ ነው። PDF Print E-mail
Sunday, 15 March 2020 15:13

ካስል (መጋቢት ፮- ፳፻፲፪ ዓ.ም) ለማችን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን

በጀርመን የካስል ደ/ቀ/ መድኃኔዓለም ካህናትና ምእመናን በማበራዊ መገናኛ ብዙሃን ምሕለላናሎት አደረሱ።


በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአብዛኞቹ የውጭ አገራት ህዝባዊና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች

መታገዳቸውን ተከትሎ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን መሰባሰብ ባይችሉም በስካይፔ በቫይበርና በፌስቡክ

ተገናኝተው አምላካችን ምህረቱን እንዲያወርድ ሲማፀኑ አርፍደዋል።

 

እዚህ በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናት የሚካሄደው ሳምንታዊ የቅዳሴ አገልግሎት

እንዳይስተጓጎል በራዊ መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም የመዝሙር የጸሎት የትምህርትና የቅዳሴ አገልግሎት ሰጥተዋል።

ቁጥራቸው የማይናቅ ምእመናንም በተቻላቸው መጠን የአገልግሎቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል።


በተለይ በጀርመን የካስል ደ/ቀ/መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ምሥጢር ዶክተርሩይ ኤርምያስ

መሪነት በተከናወነው የጸሎት የምሕለላና የስብከት አገልግሎት ምእመናን በዓለማችን የተከሰተው ወረርሽኝ

እንዲወገድና አምላካችን በምህረቱ እንዲጎበኘን በያለንበት ተግተን መጸለይ እንዳለብን አስገንዝበዋል።


እግዚአብሔር ቸርነቱ የማያልቅበት አምላክ በመሆኑም ባለፉት ዘመናት የተከሰቱ ደዌያትን እንዳስወገደልን

አሁንም ምህረቱ እንዳይለየን መጾም መጸለይ መስገድና ምሕለላችንን አጠናክረን እንድንቀጥልም አሳስበዋል።


በተለያዩ መካነ ድሮች አማካኝነትም በአባታችን በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሰረት የትንሳኤ ጾም አራተኛ ሳምንት

መጻጉዕን አስመልክቶ ወቅታዊውን ወረርሽኝ ያካተተ ስብከትም ተሰጥቷል።


በዓለማችን የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ በአውሮፓ የሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሀገረ ስብከት

ጳጳሳት ሳምንታዊ የቅዳሴና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ መወሰናቸው ይታወቃል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

 

 
« StartPrev12345678NextEnd »

Page 1 of 8

ሌሎች ድረ ገጾች

Featured Links:

feed-image Feed Entries


Powered by Medhanealem.