የካርልስሩኸ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የደብር ስያሜ ተሰጠው። Print
Saturday, 24 January 2015 21:42

ካስል ጥር ፲፮/፳፻፯ ዓ.ም (ጀርመን) በጀርመን አገር የሚገኘው የካርልስሩኸ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ወር ጀምሮ የካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ። የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪም መልአከ ስብሐት የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቷቸዋል።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአድባራትና የገዳማት ትክልና አመሠራረት ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ ደብር ወይም ገዳም የራሱ የሆነ ስያሜ እንዲኖረው ይደረጋል።


በዚህም ምክንያት የደብሩን አመሠራረትና እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት በኢ/ኦ/ተ/ቤ የደቡብ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሙሴ ውሳኔ መሠረት ስያሜው እንደተሰጠም ከሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ከመጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

 

በተያያዘ ዜናም የደብሩ አስተዳዳሪ ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት የነበረው የማዕረግ መጠሪያ ተለውጦ መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ ተብለው እንዲጠሩ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ወስነዋል።

 

መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ                                                                            መጋቤ ሥርዓት በሪሁን ጌታቸው


የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ በአገልግሎት ወደ ጀርመን ሀገር ከመጡ ጀምሮ በደብራቸውና በየአድባራቱ በመዘዋወር እየሰጡት ያለውን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲሁም ተተኪ ሕፃናትን ሰብስበው በማስተማር የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለማፍራት እያደረጉ ያለውን ጥረት ለማበረታታት በማሰብ የማዕረግ ስያሜው እንደተሰጣቸውም ታውቋል።


በተጨማሪም የካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና ለደብሩ መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱት አቶ በሪሁን ጌታቸውም የረጅም ጊዜ ያላሰለሰ ትጋታቸውን ታሳቢ ያደረገ፥ ለአገልግሎታቸው የሚመጥን መጋቤ ሥርዓት የተሰኘ የማዕረግ ስም እንደተሰጣቸው ማወቅ ተችሏል።


በመጨረሻም የደብሩም ስያሜም ሆነ የአስተዳዳሪውና የምክትል ሰብሳቢው የማዕረግ ክብር የተሰጠው አገልግሎት በመጠናከሩና አመርቂ ሥራ በመሠራቱ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የገለጹ ሲሆን እዚህ ደረጃ የደረሰው አመርቂ እንቅስቃሴ ይበልጥኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ ምክርና መመሪያ ሰጥተዋል። የዝግጅት ክፍላችንም ለደብሩ ሁለንተናዊ ዕድገት መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!